ቁልፍ የሀገር መሠረተ-ልማቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ - ብሔራዊ መረጃ ማዕከል
ቁልፍ የሀገር መሠረተ-ልማቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ
ቁልፍ የሀገር መሠረተ-ልማቶችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በቁልፍ መሠረተ-ልማቶች በተለይም በኤሌክትሪክ መሠረተልማቶች ላይ የሚደረጉ ዝርፊያዎችን፣ ውድመቶችንና አሻጥሮችን በተመለከተ የሠራው ጥናት የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ቀርቦ ውይይት መደረጉን አገልግሎቱ አመልክቷል፡፡
በቀረበው ጥናት ፀረ-ሰላም ኃይሎችና በአሸባሪነት የተፈረጀው ሸኔ በመከላከያ ሰራዊቱና በክልል የፀጥታ ኃይሎች የሚደርስባቸውን ምት መቋቋም ሲሳናቸውና ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር የነበራቸው ቅዠት ከንቱ መሆኑን ሲያረጋግጡም የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶችን በማውደም በህዝብና በመንግስት መካከል መቃቃር እንዲኖር አበክረው እየሠሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
አንዳንድ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ሠራተኞችና ስግብግብ ነጋዴዎችም በመሠረተ-ልማቶቹ ዝርፊያ ላይ እጃቸው እንዳለበት የጠቆመው ጥናቱ፤ በደረሱ ውድመቶችና ስርቆቶች ከ732 ሚሊዮን ብር በላይ የሀገር ሀብት ለኪሳራ መዳረጉንም አመልክቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የችግሩን አሳሳቢነት በውል በመገንዘብ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የሚጠነስሱትን ሴራ ለማምከን ተናቦና ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡
ሀገርን የማፍረስ እኩይ ዓላማ አንግበው በቁልፍ መሠረተልማቶች ላይ ውድመትና ስርቆት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር ሀብቶች ላይ የሚደርሱ ውድመቶችንና የሚጎነጎኑ አሻጥሮችን በወቅቱ በመገምገም ተመጣጣኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ብሔራዊ ግብረ ኃይል ሊቋቋም እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው፤ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በቁልፍ ተቋማትና መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ጉልህ የብሔራዊ ደኅንነት አንድምታ ስላላቸው እንደ ተቋም ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ስምሪት ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ተቋማትና መሠረተ-ልማቶች በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እና በሚሰጡት አገልግሎት ተመዝነው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም፤ በአሸባሪዎችና ጽንፈኛ ኃይሎች ወሳኝ ኢላማ ተደርገው በመወሰዳቸው ተግዳሮቶች ማጋጠማቸው አንዳልቀረም አስገንዝበዋል፡፡
በመሠረተ ልማቶች ላይ የተደቀኑ ስጋቶችን ለመቀልበስ የሚያስችል የተቀናጀ የመረጃ ስምሪት በማድረግ ስጋትን መለየት፣ ማጥናት እና መረጃዎችን አደራጅቶ በወቅቱ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የሚከናወነው የተልዕኮ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሲሳይ አመልክተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ውድመቶችንና ስርቆቶችን ለመከላከል ክልሎች ኃላፊነት ወስደውና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፤ የኃይል መቆራረጥ በክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በትኩረት መሥራትና ህዝቡ መሠረተ- ልማቶችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅ በማድረግ በኩል በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በመድረኩ እንዳብራሩት፤ በኤሌክትሪክ መሠረተ- ልማቶች ላይ ወንጀሎች እየተፈፀሙና ተግዳሮቶችም እያጋጠሙ በዘርፉ ከፍተኛ ትርፍ ተገኝቷል፡፡ ችግሮች የተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሠረተ-ልማቶችን በአስቸኳይ ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደገለፁት፤ ቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ወደታች በማውረድ ውይይት ሊደረግባቸውና እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ወደ ሥራ ሊገባ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ አካላት ቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኃላፊነት ወስደው እንዲንቀሳቀሱና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን እንዲከላከልና ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመሠረተ-ልማቶቹ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታትም ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡
ቁልፍ ተቋማት እና መሠረተ- ልማት ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዲሁም በእያንዳንዱ ክልል የሚተላለፈውን የኃይል ተሸካሚ አስተማማኝ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነትን በአግባቡ ያልተወጡ የአስተዳደር አካል እና የማህብረሰብ ክፍል ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋት በጥናቱ ከተጠቆሙ መፍትሄዎች መካከል እንደሚገኙበት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡